6ኛው አገር አቀፍ የኅብረት ስራ ኤግዚብሽንና ባዛር ተከፈተ

Posted by:Anonymous (not verified)
11 February 0

በፌዴራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በየዓመቱ የሚካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ የኅብረት ስራ ኤግዚብሽንና ባዛር-2011 “የኅብረት ስራ ማህበራት ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት! ” በሚል መሪ-ቃል የካትት 01/2011 ዓ.ም በይፋ ተከፍቷል፡፡

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ እንዳሉት፣የኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲቋቋሙ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣የአባላት ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣አላስፈላጊ የገበያ ትስስርን በማሳጠር ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ሀገሪቱ ያስቀመጠችውን ከግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው መዋቅራዊ ለውጥ የኅብረት ሥራ ማህበራት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚችሉ እምነት በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ የልማታችንና ፈጣን ዕድገታችን የማይተካ አስተዋጽኦ የሚያደርገውና ዘመናዊ አምራች ዘርፍ በመሆን የዕድገት ምንጭ ለሚሆነው ግብርና ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡ሚኒስቴር ዴኤታዋ አያይዘውም ህዝባችን ከአስከፊ የኑሮ ደረጃ ለማላቀቅ መንግስት በቀየሳቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዊች መካከል የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲያችን አንዱ መሆኑን ገልፀው በሂደቱም ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የግብርና ኅብረት ስራ ማህበራት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡ የግብርና-መር ኢንደስትሪ ትራንስፎርሜሽንን በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ የኅብረት ሥራ ማህበራት አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማላመድና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እንዲሁም በእርሻ መካናይዜሽን እና ግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በማስፋፋት ረገድ የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የኤግዚብሽንና ባዛሩ ዋና አላማም የኅብረት ስራ ማህበራትን እርስ በርስና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በማስተሳሰር በግብርና ምርቶች ግብይት ገበያውን ማረጋጋት እና የአምራችና ሸማቹ የጋራ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡

የፌዴራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው የተዘጋጀው ኤግዚቢሽና ባዛር በአገራችን ስኬታማ ሥራ የሠሩ ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ ከሸማቾች፤ ከግብርና ምርት አቀነባባሪዎች (Argo-processors)፣ ከኤክስፖርተሮች፤ የግብርና ምርት ከሚገበያዩ አካላት ጋር ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር በመፍጠር በከተሞች አካባቢ በፍጆታ ሸቀጦች እና በግብርና ምርቶች ግብይት ላይ የሚታየዉን የዋጋ ንረት ሸማቹን ከአምራቹ ጋር በማገናኘት ገበያውን ለማረጋጋት እና ለዘርፉ ዕድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዘርፉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ አበረታች ሥራዎች ከ85 ሺህ በላይ መሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ 388 የኅብረት ሥራ ዩኒዮኖችና 3 የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖችን በማደራጀት በርካታ ሴቶችና ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ኅብረት ስራ ማህበራቱ እንቅስቃሴያቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከሩ በመምጣት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማንቀሳቀስና ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ እንደተቻለ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል ። የኩነት ዝግጅቱ አርሶ አደሩ ካመረተው ምርት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት የገበያ ትስስር በመፍጠር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡ በዚህ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ የኅብረት ሥራ ማህበራትና ግብዓት አቅራቢዎች፣ ገዢዎች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ የንግድ ድርጅቶችና ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር በጋራ የሚሰሩ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ እስከ የካቲት 06/2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ አዘጋጁ የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡