10ኛው የባህል ሳምንት ተከፈተ

Posted by:Mariawit
01 February 0

በአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀው እና ከጥር 24-26/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄደው 10ኛው የባህል ሳምንት በይፋ ተከፍቷል፡፡ የባህል ሳምንቱ በአዲስ አ.አ ከተማ ባሉ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች በየደረጃው ከጥር 08/2011 ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱንና በአዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄደው ዝግጅትም የዝግጅቱ ማጠቃለያ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፤ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረ/ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገልፀዋል፡፡

በዓሉ ባህል-ለህዝቦች ሠላምና አንድነት በሚል መሪ ቃል የሚከበር እና ዓላማውም በባህሉና ቅርሱ የሚኮራና ለስራ የሚነሳሳ ትውልድ ለመገንባት መሆኑን ፤ ከዚህ በተጨማሪም በከተማችን የሚገኙትን የተለያዩ የህብረተሰቦች መገለጫ የሆኑትን ቅርሶች የምናስተዋዉቅበት እንዲሁም የዕደ ጥበብ የባህል ኢንዱስትሪ ዉጤቶች ለህብረተሰቡ የምናሳይበት ሲሉ የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል የእለቱ የክብር እንግዳ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት በመክፈቻ ንግግራቸው ፤ ትውልዱን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና መጤ ባህሎች በመጠበቅ ለማነፅ የእንዲህ ዓይነት ባህላዊ ዝግጅቶች አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ለዚህም መሳካት ሁላችንም ሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል ፡፡

በበዓሉ የተለያዩ የግጥም ፣ የሙዚቃ ፣ የዉዝዋዜ ዉድድሮች እንዲሁም ፓናል ዉይይት የሚኖር ሲሆን በአጠቃላይ በዓሉ በሚከናወንባቸው ቀናትም በአራቱም ቲያትር ቤቶች የሚታዩ ቲያትሮች ለከተማችን ነዋሪዎች በነፃ እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡