7ኛው የኅብረት ስራ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተጠናቀቀ

Posted by:Mariawit

በፌዴራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ አስተባባሪነት በኤግዚቢሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር በስኬት ተጠናቀቀ፡፡ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የመዝጊያ ስነስርዓት ላይ በተገለፀው መሰረት ኅብረት ሥራ ማህበራትንና ሌሎች የግብይት ተዋኒያንን ገጽ-ለገጽ በማገኛኘት ጥር 29 ቀን 2012 ዓ/ም የተጀመረው 7ኛው ሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከአራቱም ማዕዘን የተሰባሰቡ 156 በላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ኅብረት ሥራ ማህበራት እና ከ22 የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢዎች የተሳተፉበት፣ ከ40 ሺህ በላይ ጎብኝዎችና ሸማቾች በቀጥታ ተጠቃሚ የሆኑበት ስኬታማ ኤግዚቢሽንና ባዛር እንደነበር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ኡስማን ሱሩር ተናግረዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ ፤በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ም/ሚኒስትር የተከበሩ አቶ መስፍን ቸርነት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም፤ በኤግዘቢሽንና ባዛሩ የተሳተፉት ኅብረት ሥራ ማህበራት የአባላትን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት ሀገራዊ ብልጽግና መረጋገጥ ላይ ያላቸውን ብርቱ ክንድ ያሳረፉበት እና ለሀገራችን የሰላም ግንባታ መረጋገጥ ሚናቸውን እውን ያደረጉበት ነው ብለዋል፡፡

የተከበሩ አቶ መስፍን ቸርነት ይህን ሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽን፤ ባዛርና ሲምፖዚየም ላዘጋጁት እንዲሁም ዝግጅቱን በፋይናንስ፤ በሀሳብ እና በቁሳቁስ በመደገፍ ከፌደራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ ጎን በመቆም የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ተቋማትና ግለሰቦች ያላቸውን ታላቅ አክብሮትና ምስጋና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስትና በራሳቸውም ስም በማቅረብ በቀጣይ እንዲህ አይነቱ ፍሬያማ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው በማሳሰብ የዝግጅቱን መዘጋት በይፋ አብስረዋል፡፡

በመጨረሻም የክብር እንግዳው ከኤጀንሲው የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለተሳተፉ ድርጅቶችና የህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት የተሳትፎና የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡ ድርጅታችን ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅትም በዝግጅቱ አጠቃላይ ሂደት ላደረገው ድጋፍ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡