7ኛው ሀገር አቀፍ የኀብረት ሥራ ኤግዚቢሽንና ባዛር እየተካሄደ ነው፡፡
በፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ አዘጋጅነት የተሰናዳውና የኅብረትሥራ ግብይት ለሰላም ግንባታ! “COOPERATIVE MARKETING FOR PEACE BUILDING!” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 29 እስከ የካቲት 4 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ስራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛር በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ፡፡ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የኤግዚቢሽንና ባዛሩን ዓላማ አስመልክተውንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ኡስማን ሱሩር፤ የአምራቾች ኀብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን በማስተዋወቅና ከተጠቃሚ ጋር ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ለማህበረሰቡ ምሬት ምክንያት የሆነውን ኢ-ፍትሃዊ ግብይትን በማክሰም ጤናማ ግብይት መፍጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዓመቱን መሪ ሀሳብ የተመረጠበትን እሳቤም ሲያብራሩ ኀብረት ሥራ ማህበራት ቀዳሚ ተግባራቸው የገንዘብ ትርፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ቅድሚያ ለሰው ልጆች ክብ፣ ለፍትሃዊነት እኩልነትና የአብሮነት መገለጫዎች በመሆናቸውእና በአንድነት በመቆምም የሰላም ዘብ መሆናቸው ለማሰገንዘብ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ሲናገሩ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከመላው ሀገሪቱ የሚመጡ 150 አምራች የኀብረት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውን በጥራትና በበቂ መጠን እንደሚያቀርቡና በዚህም ከሸማቾች ኀብረት ሥራ ማህበራት፣ ከተጠቃሚ ተቋማትና ከግብዓት አቅራቢ ኢንዱስትሪዎች ጋር ዘላቂ የግብይት ትስስር እንደሚፈጠር ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ከቡር አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው በኤግዚቢሽንና ባዛሩ መክፈቻ ንግግራቸው የህብረት ስራ ማህበራት ለሚያከናውኑት ሁሉ ዓቀፍ ተግባራት መንገስት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራና ህብረት ስራ ማህበራቱን የሚደግፍ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር አካል የሆነው ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ጥር 28 ቀን 2012 በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የህብረት ስራ ማህበራት አባላትና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት እንደተካሄደና በዚህም የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት የኀብረት ሥራ ማህበራት ምርጥ ተሞክሮና ልምድ ልውውጥ በማድረግ ወደ ሌሎች ለማስፋት አቅም የፈጠሩበት መድረክ ሆኖ መጠናቀቁ ተገልጧል፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባና አካባቢው ማህበረሰብ ከጥር 29 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 4 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በመገኘት የኀብረት ሥራ ማህበራት ጥራት ያላቸው የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያዩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡