የ2012 ዓ.ም የገና ባዛርና ፌስቲቫል በይፋ ተከፈተ
“ሰላም የገና ባዛርና ፌስቲቫል-2012“በሚል መሪ ቃል በኮሜርሺያል ኖሚኒስ ኃ/የተ የግ ማ. የተዘጋጀው እና ከታህሳስ 04-27/2012 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቀው ፣ የገና ባዛርና ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ቅዳሜ ታህሳስ 04 /2012 ዓ.ም በድምቀት ተከፈተ፡፡
በመክፈቻው ስነ-ስርዓት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሜርሺያል ኖሚኒስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ዋቅ ቶላ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ኮሜርሺያል ኖሚኒስ ይህንን የገና ኤግዚቢሽንና ባዛር በኢትዮጵያ ታላቁ ሁነት እንዲሆን ሲያዘጋጅ ሶስት ዓላማዎችን ይዞ መሆኑን እነርሱም ሸማቹን ከሻጩ የማገናኘት፤የሰላምን ፋይዳ በኪነጥበብ የማስረፅ እና ድርጅታቸውን ይበልጥ የማስተዋወቅ መሆኑነን ገልጸው በተለይም ሰላማችንን በማስጠበቅ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በሌላም በኩል የዝግጅቱ አስተባባሪ የሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አድርሴ በውጭ ሃገራትና በሃገር ውስጥ ያገኘነውን ልምድ በማቀናጀት ያዘጋጀነው ዝግጅት ለሁነቱ ታላቅ ድምቀት እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑንና ይህንን ሃላፊነት እንደምንወጣው በማመን ዝግጅቱን እንድናስተባብር ያደረገውን ድርጅትና የቦርድ አባላት እንዲሁም ለዝግጅቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድጋፍ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ብዙነሽ መሰረት የበዓሉን መከፈት የሚያበስረውን ባህላዊ ሪቫን በመቁረጥ ባዛሩን በይፋ ከፍተዋል፡፡
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለሚቀጥሉት 23 ተከታታይ ቀናት ግማሽ ሚሊዮን ጎብኚዎች ይጎበኙታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎንም የበጎ አድራጎት ስራዎች እንደሚከናወኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡