የማዕከሉ ሠራተኞች በ”አረንጓዴ አሻራ“ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተሳተፉ፡፡

Posted by:Mariawit
01 August 0

ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ”ችግኝ ተከላ ለዘላቂ ልማት!“ በሚል መሪ ቃል ስር የተቀናጀ ዝግጅት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ ለሚገኙት የልማት ድርጅቶች ለችግኝ መትከያነት ባመቻቸው በተለምዶ ”ቆሼ“ በሚባለው ቦታ ላይ በመገኘት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አከናውኗል፡፡

በክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው እና ሃምሌ 22/2011 ዓ.ም ደግሞ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ፕሮግራም ላይ ሁሉም አሻራውን እንዲያሳርፍ የተላለፈውን ጥሪ ተግባራዊ ለማድረግ የማዕከሉ ሰራተኞችና የማህበራት አባላት ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡

በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ማጠቃለያ ላይ የስራ መመሪያ የሰጡት የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ ፤ቀደም ሲል የማዕከሉ ሰራተኞች በክረምት ስራዎች ዕቅድ ውስጥ ችግኝ ተከላን በማካተት በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ እና በማዕከሉ አጥር ዙሪያ የተተከሉትን ችግኞች መንከባከቡ እንዳለ ሆኖ ዛሬ በተሳተፍንበት ሃገር ዓቀፍ ፕሮግራም የተተከሉትን ችግኞች በየወሩ በባለሙያ የመንከባከብና በየሩብ ዓመቱ ደግሞ በማኔጅመንት አባላት ደረጃ በቦታው በመገኘት የመስክ ምልከታ በማድረግ የችግኞቹን ሁኔታ በማየት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡