ታላቁ የ2012 ዓ.ም እንቁጣጣሽ -ኤክስፖ ተከፈተ

Posted by:Mariawit
18 August 0

በኢዮሃ ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንትስ ኃላ.የተ.የግል.ማህ. አዘጋጅነት የተዘጋጀውና ከነሃሴ 11/2011ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 26 ቀናት የሚዘልቀው ታላቁ የ2012 እንቁጣጣሽ-ኤክስፖ በኤግዚቢሽን ማዕከል በድምቀት ተከፈተ፡፡ በኤክስፖው መክፈቻ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው በመክፈቻ ንግግራቸው፤እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት የአንድነታችንና የአብሮነታችን መገለጫ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡በሌላም በኩል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በም/ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊው ክቡር ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ በበኩላቸው በከተማዋ ለሚደረጉ ተመሳሳይ ዝግጅቶች የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደሚቀጥል እና ይህም የከተማችንን ብሎም የሃገራችንን ገፅታ የምንገነባበት በመሆኑ ይህንን ደማቅ ዝግጅት በማዘጋጀታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ ለአዘጋጁ ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንትስ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ በማዕከሉ የኤግዚቢሽንና ፌስቲቫል ታሪክ የዘንድሮውን የ2012 እንቁጣጣሽ ኤክስፖ የሚያህል በደረጃው ከፍ ያለ እና ማዕከሉንም ያስዋበ ዝግጅት ያልታየ በመሆኑ ለዚህ ዝግጅት መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉ ባለሙያዎች ድርጅቶች በተለይም ለሄንከን ኢትዮጵያ ያላቸውን ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም የዘንድሮው በዓል ለአረንጓዴ አሻራ መታሰቢያ እንደሚሆንና ማዕከሉም በዚህ ሳምንት ለአረንጓዴ አሻራ ተግባራዊነት በመቅረፅና በዲጂታል ባነሮች በማሳተም ተጨማሪ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን እያጠናቀቀ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በ2012 ዓ.ም እንደሚጀመር የሚጠበቀው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ፕሮጀክት ግንባታ በሃገራችንን በዘርፉ ከፍተኛ ቴክኖሊጂን የሚጠቀምና ከተማችንን ስማርት ሲቲ በሚባል ደረጃ የሚያሳድግ እንደሆነ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይንንትና ኤቨንትስ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲራጅ ዋሲሁን እንዲህ የደመቀ ዝግጅት ለማዘጋጀት ሲያስቡ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተለያየ ሁኔታ የደገፏቸውን ድርጅቶችና ተቋማት በተለይም የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን በማመስገን ኢዮሃ አዲስ የአ.አ ከተማ አስተዳደር ለደሃ ተማሪዎች ግብዓት የሚውል የትምህርት ቁሳቁስ ባቀረበቀወ ጥሪ መሰረት 10ሺህ ደብተር እና 2 ሺህ እስክሪብቶ በተጨማሪም የአረጋውያንን ቤት ማደሻ 150 ሺህ ብር ስጦታ ያበረከተ ሲሆን ስጦታውንም ክቡር ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ ተረክበዋል፡፡

በዘንድሮው የእንቁጣጣሽ ኤክስፖ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ተሳታፊዎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ በ1000ስኒ የታጀበ የጀበና ቡና ማፍላት ስነ-ስርዓትና የሴባስቶፖል መድፍ እንዲሁም በዋናው መግቢያ በር ባህላዊ የሙዳይ አምሳያ ቅርፅ ተዘጋጅቶ በመቅረቡ ለዝግጅቱ ተጨማሪ ድምቀት ሆኗል፤ ኤክስፖው እስከ ጳጉሜን 6/2011 ዓ.ም ድረስ ሞቅ ደመቅ እንዳለ እንደሚቆይ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡