ታላቁ የገና ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ

Posted by:Mariawit
19 December 0

በሃበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተዘጋጀው ከታህሳስ 06-28/2011 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቀው ፣ 500 የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር የንግድ ድርጅቶች የሚሳተፉበት እንዲሁም ልዩ ልዩ የግብይትና የመዝናኛ ዝግጅቶችን ያካተተው የዘንድሮው የገና ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ቅዳሜ ታህሳስ 06 /2011 ዓ.ም በድምቀት ተከፈተ፡፡

በመክፈቻው ስነ-ስርዓት የሃበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አዶኒክ ወርቁ እንደተናገሩት  ድርጅታቸው ሃበሻ ዊክሊ ይህንን የገና ኤግዚቢሽንና ባዛር በኢትዮጵያ ታላቁ ሁነት እንዲሆን በተደረገው ጥረት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የሚቀርበውን የዳይኖሰር ትዕይንት (ጁራሲክ ፓርክ) ማስመጣታቸው እንዳለ ሆኖ በሻማ የተሰራውም የገና ዛፍ ለሁነቱ ታላቅ ድምቀት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሃላፊ እና የክቡር ከንቲባው ተወካይ አቶ አብዱል ፈታህ ዩሱፍ በበኩላቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ህዝቦችን ለማቀራረብ  የሚረዱ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት እንደሰጠ እና መሰል ዝጅቶችን ለማከናወን እንዲያስችልም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል እየተገነባ መሆኑን በዋቢነት ጠቅሰው ይህ ዝግጅት ለሀገር ገፅታ ግንባታም አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የተዘጋጀውን ሪባን በመቁረጥ ዝግጅቱን በይፋ ከፍተዋል፡፡

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ታህሳስ 05/2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ላበረከቱት አስተዋፅኦም ምስጋና የቀረበ ሲሆን  800 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸውን የመሸጫ ቦታዎች ለ10 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዘጋጁ ሃበሻ ዊክሊ በነፃ ከመስጠቱም በላይ ለአነስተኛና ጥቃቅን አንቀሳቃሾች በግማሽ ዋጋ እንዲስተናገዱና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩን ግማሽ ሚሊዮን ጎብኚዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡