ታላቁ የገና ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ
በሃበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተዘጋጀው ከታህሳስ 06-28/2011 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቀው ፣ 500 የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር የንግድ ድርጅቶች የሚሳተፉበት እንዲሁም ልዩ ልዩ የግብይትና የመዝናኛ ዝግጅቶችን ያካተተው የዘንድሮው የገና ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ቅዳሜ ታህሳስ 06 /2011 ዓ.ም በድምቀት ተከፈተ፡፡
በመክፈቻው ስነ-ስርዓት የሃበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አዶኒክ ወርቁ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ሃበሻ ዊክሊ ይህንን የገና ኤግዚቢሽንና ባዛር በኢትዮጵያ ታላቁ ሁነት እንዲሆን በተደረገው ጥረት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕይታ የሚቀርበውን የዳይኖሰር ትዕይንት (ጁራሲክ ፓርክ) ማስመጣታቸው እንዳለ ሆኖ በሻማ የተሰራውም የገና ዛፍ ለሁነቱ ታላቅ ድምቀት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡