ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ተከፈቱ!

Posted by:Mariawit
14 May 0

በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በየዓመቱ ከሚዘጋጁት የንግድ ትርኢቶች መካከል አንዱ የሆነው ዓለም ዓቀፍ የግብርናና የምግብ የንግድ ትርኢት ለ12ኛ ጊዜ የተከፈተ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን በህክምና ጉዳይ ላይ ያተኮረው ዓለም ዓቀፍ የህክምና የንግድ ትርኢትደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንቦት 1/2011 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡

125 የሀገር ውስጥና እና ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት በጥምረት የተከፈቱት እነዚህ የንግድ ትርኢቶች የንግዱን ማህበረሰብ ለማቀራረብ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የም/ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ መንግስት እንዲህ ዓይነቱን የንግድ ትርኢት ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ቁርጠኛ መሆኑን እና የመንግስትንና የንግዱን ማህበረሰብ አጋርነት መጠናከር ቀዳሚው የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት ጨምረው አሳስበዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የንግድ ትርኢቱ ዓላማ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ሀገር አቻዎቻቸው ጋር ውይይት በማድረግ ዘላቂነት ያለው የቢዝነስ ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር መሆኑን የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ተናግረዋል፡፡

የንግድ ትርኢቶቹ እስከ ግንቦት 05/2011 ዓ.ም ለጎብኚዎች ክፍት መሆናቸውናና ጎብኚዎችም በነፃ መጎብኘት እንደሚችሉ አዘጋጁ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታውቋል፡፡