ከተማ ዓቀፍ የባህልና ኪነጥበብ ሳምንት አውደ ርዕይ ተከፈተ፡፡

Posted by:Mariawit

ባህልና ኪነጥበብ ለህዝቦች ሰላምና አንድነት! በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ፤በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት የተዘጋጀውና ከጥር 22-24/2012 ዓ.ም የሚቆየው 11ኛው ከተማ ዓቀፍ የባህልና ኪነጥበብ ሳምንት አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በድምቀት ተከፍቷል፡፡

በመክፈቻው ስነስርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት የበዓሉን መዘጋጀት አስፈላጊነት ሲገልፁ ፤ያልተጠቀምንባቸውን ኪነጥበባዊ ክዋኔዎች ለመጠቀምና የባህልንና የኪነ ጥበብን ሃብቶቻችንን በመንከባከብና ለህዝቦች ሰላምና አንድነት ለመጠቀም እንዲቻል በዚህም ሃገራችንን ወደ ቀደመ ስምና ክብሯ ለመመለስ የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ ነወ ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ ዶ/ር እልፍነሽ ሃይሌም በበኩላቸው የባህልና ቱሪዝም ሃብታችንን በመጠቀም የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል እምነታቸው እንደሆነ እና ለዚህም ሚ/ር መ/ቤታቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ግርማን ጨምሮ በርካታ የጥበብ ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን ፤ በባህል ሳምንቱ ም በአዲስ አበባ የሚገኙ ቴያትር ቤቶች እና የእደጥበብ አምራቾች የባህል ምርቶች ባዛር ከመካሄዱም በተጨማሪ በአማተር የኪነጥበብ ክበባት በየቀኑ ጥበባዊ ትዕይንት ውድድር እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

በሌላም በኩል በምግብና የባልትና ውጤቶች እንዲሁም በቤትና ቢሮ ዕቃዎች ፈርኒቸር ማምረት ላይ የተሰማሩ በወጣቶችና ሴቶች የተደራጁ የኢንተርፕሪዝ አንቀሳቃሾችምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ ታድመዋል፡፡
የባህል ሳምንቱ በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ደምቆ እስከ ጥር 24/2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ አዘጋጆቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡