ሃላል ኘሮሞሽን ከበጎ አድራጎት ጋር የተያያዙ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተገለጠ

Posted by:Mariawit
12 June 0

በየዓመቱ የሮመዳንን ፆም ተከትሎ የሚዘጋጀው ኢድ ኤክስፖ ከሰኔ 06 እስከ ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚከናወን የዝግጀቱ አስተባባሪዎች ለማዕከሉ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት አገልግሎት ገለጹ፡፡ የሮመዳንን ፆም ፍቺ (ኢድ አልፈጥር) አስመልክቶ በየዓመቱ በሚከናወነው በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከ300 በላይ  ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ የባዛሩ መግቢያ ቲኬት ለ13ቱም ቀናት ዕጣዎች የሚኖሩት ሲሆን ሃጅ ደርሦ መልስን ያካተተ እና ሌሎች ታላላቅ ሽልማቶች እንደሚኖሩትም ተጠቁሟል፡፡ የሃላል ኘሮሞሽን አዘጋጅ አቶ ፈይሰል ከማል እንደተናገሩት "የዘንድሮውን የኢድ ባዛርን ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ቀደም ሲል ከቀይመስቀል ማኀበር እና ከኦቲዝም ጋር በተያያዘ እናከናውናቸው የነበሩትን የበጎ አድራጎት ስራዎች ይበልጥ በማጠናከር ዘንድሮም ከኩላሊት ህመምተኞች ማኀበር ጋር በጋራ እንሰራለን" ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የቆይታ ጊዜ ወቅት የኩላሊት ቅድመ መከላከል ምርመራ በነፃ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡ ለ6ኛ ጊዜ ለሚከናወነው ኢድ ኤክስፖ ኤግዚቢሽንና ባዛር ማዕከሉ ቁጥር ሦስት አዳራሽን ለመስገጃ በነፃ ያቀረበ መሆኑን ከሽያጭ ክፍል የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡